የተገራ ንግግር በማድረግ ተቀባይነትና ሞገስን እናግኝ

የተገራ ንግግር በማድረግ ተቀባይነትና ሞገስን እናግኝ ሠዎችን ለማስደመም ብለን ብዙ በተናገርን ቁጥር ይበልጥ ሞገሣችን ይቀንሳል፡፡ በእነሱም ላይ የአለን ተደማጭነት ይወርዳል፡፡ ታላላቅ ሠዎች ትንሽ በመናገር ነው የሠዎችን ቀልብ የሚስቡት ብዙ በተናገርን ቁጥር ሠዎች ይሠለቹናል የጅል ንግግርም እንደተናገርን ይቆጥሩናል፡፡ስለዚህ የቃላት ፀጋችን በተመረጡ ብዙ ሀሣብ በያዙ አረፍተ ነገሮች ብቻ ከርክመን እና ቀምመን አጭር መልዕክት ማስተላለፍ ልምዳችን ሊሆን ይገባል፡፡ በየትኛውም የንግግር ጊዜ አስቀድሞ የታሠበበት እና ለሁነቱ የተመጠነ መልዕክት ብቻ ማስተላለፍ ያስፈልጋል፡፡ይህ ሣይሆን ቀርቶ ማይክሮፎን በተጠጋ ቁጥር ያልተዘጋጀንበትና ያልተቆነጠጠ መልዕክት ማስተላለፍ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ምክንያቱም አፍ እንደመጣለት የሚከፍት ሠው እጣ ፈንታ በሌሎች ዘንድ ሞገስ አልባ እንዲሆን ራሡን አሣልፎ የመስጠት እድሉ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ ነው፡፡

የቃላት ፀጋ በአግባቡ ስንጠቀም በህዝብ ፊት ተቀባይነትን ማግኘታችን እርግጥ ሲሆን ይህን ሐብት ዝም ብለን በአልተገባ መንገድና በእዝላልነት ጥቅም ላይ ለማዋል ከሞከርን በሠዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት ከቶ አይቻለንም፡፡ ለዚህም ነው ታዋቂው ደራሲ ሮበርት ግሪኔ ቃላትን መቆጣጠር የማይችል ሠው እራሱን መቆጣጠር አይችልም፡፡ ራሱን የማይቆጣጠር ሠው ደግሞ ክብር እና ተቀባይነት ይሸሸዋል የሚሉን፡፡